(የኦነግ-ኦነሠ ጋዜጣዊ መግለጫ)
የኦሮሞ ነጻነት ግንባር - የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (ኦነግ-ኦነሠ) የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በታህሳስ 2021 በከረዩ የኦሮሞ የገዳ መሪዎች ላይ የተፈጸመውን አሰቃቂ ግድያ አስመልክቶ ጉዳዩን በማጣራት እና መረጃና ማስረጃዎችን በማሰባሰብ ረገድ ያደረገውን ጥረት በደስታ ይቀበላል። በኛ በኩል በኦሮሚያ ምስራቅ ሸዋ ዞን የተፈፀመውን ጭፍጨፋ በጊዜው በርካታ ታማኝ የውስጥ እና የውጭ ምንጮች ላይ በመመስረት ጭፍጨፋው በአገዛዙ ኃይሎች የተፈፀመ መሆኑን በግልጽ ተናግረን ነበር። አገዛዙ ግን በራሱ በኩል ጥፋቱን በሰራዊታችን ላይ ለማላከክ አንዳች ጊዜ አላጠፋም።
ይህ የሰብአዊ መብት ኮሚሽኑን ዘገባ ቀደም ብለን ያስቀመጥነዉን ብያኔ ያረጋገጠ ቢሆንም፣ ኦነግ-ኦነሠ ግን ሪፖርቱን ከነሙሉ ተፅዕኖዎቹ ሊመለከተው ፈልጓል። ባለፉት ሁለትና ሶስት ዓመታት በኮሚሽኑ የታተሙ ቀደምት ሪፖርቶች ሲታዩ በሀገሪቱ ውስጥ የተፈጸሙ የመብት ጥሰቶችን በተመረጡ ቦታዎች ብቻ የማጣራት እና ሪፖርት የማቅረብ ሂደት ልዩ ፍላጎት እንዳለው ግልጽ ነው። በማስረጃ ለመናገርና ያለፉትን ክስተቶች በማገናዘብ፣ ኮሚሽኑ በቅርብ ጊዜ ማይካድራ፣ በጋሊኮማ እና በጭና ስለተፈጸሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ለፖለቲካ ፍጆታ ሲባል በመንግስት አካላት የተመረጡ ሪፖርቶች እንደሆኑ እና በተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት ኮሚሽን መስፈርት ሚዛናዊ ለማስመሰል የገዳ አባቶችን ጥናት እንዳቀረበ እንገነዘባለን:: እንዲሁም ከተባበሩት መንግስታት የሰበአዊ መብቶች ጽህፈት ቤት ጋር በቅርቡ በወጣው ትግራይን በተመለከተ ሪፖርት ’’ሁሉም ተዋጊ ወገኖች ወንጀለኞች ናቸው።’’ የሚለው ፅንሰ ሃሳብ በሪፖርቱ ዉስጥ ጎልቶ እንዲወጣ በማድረግ ሂደት ኮሚሽኑ የተጫወተው አሉታዊ ሚና አይዘነጋም።
በተጨማሪም ኮሚሽኑ በሌሎች አካባቢዎች የተከሰቱ ከፍተኛ ግድያዎች እና የጅምላ ጭፍጨፋዎች ላይ ምንም ዓይነት ትርጉም ያለው የምርመራ ሥራ ያለማድረጉ ደግሞ ሌላው የወገንተኝነቱ ማስረጃ ነው። ብዙ እንደዚህ ያሉ ክስተቶች ያለፍርድ ቤት ወይም ያለምንም ዓይነት ምርመራ ተድበስብሰው ቀርተዋል። ጥቂቶቹን ለመጥቀስ ያህል፡ የኢንጂነር ስመኘው (የአባይ ግድብ ፕሮጀክት የቀድሞ ዋና ሥራ አስኪያጅ) ግድያ፣ የታዋቂው የኦሮሞ ሙዚቀኛ እና አክቲቪስት ሃጫሉ ሁንዴሳ መገደል፣ የሀገሪቱ የቀድሞ የብሄራዊ ጦር ኢታማዦር ሹም እና ባልደረቦቻቸው መገደል፣ እንዲሁም በወታደሮች፣ በፖሊስ: በአየር ሀይል በድሮኖችና በሄሊኮፕተር የተፈፀሙ የሲቪሎች የጅምላ ጭፍጨፋዎችን ከብዙ በጥቂቱ መጥቀስ ይቻላል።
ስለዚህ በብዙ ሁኔታዎች ኮሚሽኑ ያደረጋቸው ምርመራዎች እና ሌሎችን ደግሞ እንዳላየ ማለፍ ተቋሙ ለገዥው መንግሥት የሚጠቅሙና የተመረጡ ምርመራዎች ላይ ብቻ መሳተፉን በግልፅ ያመለክታል:: በቅርቡ በኛ የከረዩ የገዳ ሽማግሌዎች እልቂት ላይ የቀረበውም ዘገባ ከዚህ የተለየ አይደለም። ዘገባው ያወጣውን እውነት የምናምንና የምንቀበል ቢሆንም፣ ኢሰመኮ በገለልተኛነት የኦሮሞን የባህል መሪዎች መገደል ተሰምቶት እውነታውን ይፋ ለማድረግ ተንቀሳቅሷል ብለን ግን በፍፁም አናምንም።
ይልቁንም ዘገባው የሚከተለውን ዓላማ ለማሳካት ሲባል የተሠራ መሆኑን በውል እናምናለን።
1ኛ. አገዛዙ በአሁኑ ወቅት ብሄራዊ የምክክር ኮሚሽን የማቋቋም ድራማ እየተጫወተ መሆኑ ይታወቃል:: የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ይሄን ኢሰመኮ ያወጣውን ዘገባና ሌሎች ተመሣሣይ ድራማዎችን በመመልከት ይህ መንግሥት ገለልተኛ ኮሚሽን የማደራጀት ፍላጎት፣ ችሎታና ተአማኒነት አለው ብሎ እንዲገምት ማድረግ አንዱ ነው።
2ኛ. የኦሮሞ የገዳ መሪዎች የኦሮሞ ህዝብ ውድ እሴት መሪዎች በመሆናቸው በነሱ ላይ የተፈፀመውም ጭፍጨፋ የኦሮሞን ህዝብ ሀይማኖትና የመኖሪያ ቦታ ሳይለይ እጅጉን አስቆጥቷል:: አገዛዙ ይህን ቁጣ ማስታገስ ብቻ ሳይሆን ራሱን ሀቀኛና የኦሮሞ ህዝብ ተቆርቋሪ መስሎ ለመታየት መሞከር ደግሞ ሌላው የቀቢፀ ተስፋ አላማ ነው::
3ኛ. አገዛዙ በብልፅግና ፓርቲ የኦህዴድ ቅርንጫፍ ውስጥ ካሉ የተለያዩ ክንፎች መካከል አንዱ ላይ የፖለቲካ ነጥብ ለማስቆጠር ብሎም ለማስወገድ ነው::
ስለዚህ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን እንደስሙ ሰብአዊ ለመሆን እንዲሁም ከወገንተኝነት ፀድቶና ከገዢው ፓርቲ ተላላኪነት ወጥቶ ተአማኒ ተቋም ለመሆን ገና ብዙ መስራት የሚጠበቅበት መሆኑን እናስገነዝባለን::
ድል ለኦሮሞ እና ለተጨቆኑ ህዝቦች በሙሉ! የኦነግ-ኦነሠ ከፍተኛው ዕዝ ፌብሯሪ 5፣ 2022
Kommentare