(የኦነግ-ኦነሠ ጋዜጣዊ መግለጫ)
በኢትዮጵያ ኢምፓየር የፖለቲካ፣ የባህል እና የሃይማኖት ተቋማት የተወለደውና ያደገው ኦሮሞ ጥላቻ(ፎቢያ) ዛሬም ያለማቋረጥ ቀጥሏል። በዘር አጥፊው የአብይ መንግስት እና የኒዮ-ነፍጠኛ አጋሮቹ ተደጋጋሚ፣ የተሳሳቱ መረጃዎች እና የተንኮል ፕሮፓጋንዳ ዘመቻዎች ተጠናክረው የቀጠሉ ቢሆንም፣ የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (ኦነሠ) የኦሮሞን ህዝብ ከብሄራዊ ጭቆና ለማላቀቅ የጀመረውን ትግል በተሻለ ቁርጠኝነት እየሰራ ነው። ሰራዊታችን የሚዋጋው ከጨቋኝ ስርአቶች ጋር እንጂ ከግለሰቦች ወይም ከማንም ህዝብ ጋር እንዳልሆነ ያለመታከት ደጋግመን እንገልፃለን::
እንደ አንድ የፖለቲካ ድርጅት እና የነጻነት ሰራዊት፣ የኦሮሞን ህዝብ በተከታታይ አፋኝ መንግስታት ከደረሰበት ስቃይ በዘላቂነት ለማዳን ወጥ አላማ ያለው ሰራዊታችን በንፁሀን ዜጎች ላይ በማነጣጠር የሚያገኘው አንዳችም ፖለቲካዊም ሆነ ወታደራዊ ትርፍ የለም። ይልቁንም የህይዎት መስዋዕትነት ሳይቀር እየከፈልን ኦሮሚያን ቤቴ ብለው የሚኖሩና ንፁሀን ኦሮሞ ያልሆኑ ሰላማዊ ዜጎችንና ሌሎች ተጋላጭ ማህበረሰቦች ህልውና እየጠበቅን እንገኛለን።
ነገር ግን የኢትዮጵያን ፖለቲካ በቅርብ የሚከታተል ማንኛውም አካል የአብይ መንግስት እና የነፍጠኛ ረዳቶቹ በህዝባችን ላይ ለሚፈጽመው ግፍና በደል የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊትን ስም መሸፈኛ አድርገው እንደሚጠቀሙበት በቀላሉ መረዳት ይቻላል። ኦሮሞን ገድለው ኦሮሞውን ለሞታቸው ተጠያቂ ያደርጋሉ። በቅርብ ጊዜም በገዳ መሪዎቻችን ላይ በከረዩ የብልፅግና መንግሥት የፈፀመውን እልቂት በኦነሠ ላይ ለማላከክ ያዘጋጁት ውንጀላ፣ ተናግረው ሳይጨርሱ የቀሰሩት ጣት ወደራሳቸው መዞሩን እናስታውሳለን:: ይህ ተጎጂውን መልሶ የማሸማቀቅ ማኪያቬላዊ ስልት በመደበኛነት ሥራ ላይ ከዋለ አንድ ምዕተ አመት አልፎታል።
ትልቁ ችግር ደግሞ በአሁኑ ሰአት በኦሮሚያ ውስጥ የሚፈጠረውን ነገር በተአማኒና በሶስተኛ አካል ማረጋገጥ ፈጽሞ የማይቻል መሆኑ ነው። አለም አቀፉ ማህበረሰብ በኦሮሚያ እየተፈፀመ ያለውን አሰቃቂ ወንጀል እንዳይመረምር ለማድረግ በማሰብ ብልፅግና ክልሉን ከሌላው አለም ለሶስት አመታት ያህል በመዝጋትና ለተወሰኑ ጊዜያት እንኳ የሚሰሩ የስልክ መስመሮች እና አንዳንድ የኢንተርኔት ግኑኝነቶች ሊኖሩ የሚችሉባቸውን ዕድሎች ከልክሏል። ይህ አብይ ወንጀሉን ለመደበቅ ክልሉን በጨለማ ውስጥ የማስቀመጥ ሴራ ምንም እንኳን ሰሚ ጠፍቶ ዝምታ ቢመረጥም አለም ሁሉ ያውቀዋል የሚል እምነት አለን።
እንደተለመደው በኦሮሚያ ተፈፀመ የተባለውን አሰቃቂ ወንጀል በገለልተኛ አካል እንዲጣራ እና ወንጀለኞች በህግ እንዲጠየቁ ኦነግኦነሠ ያሳስባል። አለም አቀፉ ማህበረሰብ ኦሮሚያን ለአለም አቀፍ ሚዲያ ክፍት እንዲያደርግም በአገዛዙ ላይ ጫና እንዲያሳድር አጥብቀን እንጠይቃለን። አገዛዙ እንደሚለው ለተፈፀሙ ወንጀሎች ተጠያቂ ካልሆነ ክልሉን ከገለልተኛ ሚዲያዎች የሚዘጋበት አንዳችም ምክንያት አልነበረም።
ከዚህ ቀደም በሰጠናቸው ጋዜጣዊ መግለጫዎች ላይ ደጋግመን እንደገለጽነው የብልፅግና መንግሥት በኦሮሚያ ውስጥ ለሦስት ዓመታት የጅምላ ግድያ ሲፈጽም ቆይቷል። ይሁን እንጂ የእንደዚህ አይነት ወንጀሎች ዜና ሆነው ለህዝብ የሚወጡት አልፎ አልፎ ሲሆን ይሄውም ገዥው መንግሥት የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊትን ያለሀጢያቱ መወንጀል ሲፈልግ ብቻ ነው። እንዲያውም አገዛዙ በኦሮሚያ የሚፈጸሙ ማንኛውም ነገሮችን መደበቅ ግልፅ አቋሙ ሆኗል። በዚህ ረገድ የአገዛዙ የመገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን በህዳር ወር ላይ ኦነግ-ኦነሠ በሚንቀሳቀስበት የኦሮሚያ ክልል አካባቢዎች ምንም አይነት ዘገባ እንዳይዘግብ በመንግሥት ድጎማ ለሚሠራው ኢሳት የተባለ የአሀዳዊ ፅንፈኞች ቴሌቪዥን የፃፈውን የውስጥ ደብዳቤ ማስታወስ ይጠቅማል።
በቅርቡም ሰራዊታችንን ለመወንጀል ሲባል በምዕራብ ኦሮሚያ በሰላማዊ ዜጎች ላይ የተፈፀመውን ጭፍጨፋ በተለመደው አሰራር የህዝብ መነጋገሪያ ጉዳይ እንዲሆን መወሰኑና ከቀናት በኋላ ደግሞ ዜናውን በተለያየ መልኩ በማስተባበል ለመዝጋት ቢሞክርም በኒዮ ነፍጠኛ ተባባሪዎች በአዲስ መልኩ መነሳቱን እያየን ነው። ለመሆኑ አገዛዙ ይህን እልቂት ለምን በአደባባይ አቀረበው? የሚለው ትንሽ መብራራት ይገባዋል ብለን እናምናለን:: አብይ እና የኒዮ-ነፍጠኛ አጋሮቻቸው ከዚህ የእልቂት ዜና ቢያንስ በሚከተሉት መንገዶች የፖለቲካዊ ጥቅም ሊያገኙ አቅደዋል።
1ኛ. ቀደም ብለን እንደገለጽነው ዘር አጥፊው የአብይ መንግስት የተለየ የፖለቲካ አመለካከት ያላቸዉን ህዝቦች የማጥፋት ፖሊሲ ለማሳካት፣ የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊትን በአደባባይ በመወንጀል በኦሮሚያ ሌላ ዙር ወገኖቻችን ላይ የዘር ማጥፋት ዘመቻ እንዲፈጽም ፍቃዱን እያደሰ ነው።
2ኛ. አብይ በብልፅግና ፓርቲ ውስጥም ሆነ ውጭ ባሉ ፅንፈኛ የአማራ አጋሮቹ ላይ ጥብቅ ቁጥጥርና መግባባት እያጣ ነው። እነዚህም ተስፋፊዎች በኦሮሚያ ክልል ለጥቃት የተጋለጡ መሆናቸውንና ሊያድናቸው የሚችለው ደግሞ እሱና እሱ ብቻ መሆኑን በተግባር ማሳየት ይፈልጋል። በአሁኑ ዙር ይህንን ግብ ያሳካው የተጎጂዎችን ማንነት እንኳን ሳይለይ ነበር። የአማራ ፅንፈኞችን ጠልፎ ወጥመድ ውስጥ እንዲገቡ ለማድረግ ‘የሲቪል እልቂት’ እና ‘ኦነሠ’ን በአንድ ላይ መጥራት ብቻ በቂ ነው።
3ኛ. በኦሮሚያ የብልፅግና ቅርንጫፍ ውስጥ ያለውን አንጃ ለማጽዳት ውሳኔ ተላልፏል:: የወቅቱን ዜና ተከትሎ ኦሮሚያን የሚያስተዳድረው የፓርቲው ቅርንጫፍ ተደጋጋሚ ውንጀላ እየተሰነዘረበትና በክልሉ ሰላማዊ ዜጎችን ከጥቃት መከላከል አልቻለም የሚለው ክስ በሰፊው እየቀረበበት ይገኛል:: አብይም በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ እንዲሉ ተቀናቃኞቹን አስወግዶ የፖለቲካ የበላይነቱን ያገኛል።
4ኛ. አንዳንድ ከመንግስት ጋር የተቆራኙ የኒዮ- ነፍጠኛ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲሁ በቅርቡ በኦነሠ ላይ ተመሣሣይ ውንጀላ አቅርበዋል ። ይህንንም የሚያደርጉት ከአብይ አገዛዝ ጋር በፈጠሩት ያልተቀደሰ ጋብቻ ምክንያት ያጡትን ደጋፊ እንደገና ለማገናኘት በማሰብ ነው።
በመጨረሻም የቀረበው ክስና ውንጀላ በታማኝና ገለልተኛ አካል እንዲጣራ እና አጥፊዎችም በህግ እንዲጠየቁ በድጋሚ ጥሪያችንን እናቀርባለን። ለተጎጂዎች ፍትህን እና ለቤተሰቦቻቸው በቂ ካሳ እንዲከፈል እንዲደረግ እየጠየቅን ይሄንን ገለልተኛ ምርመራ ለመደገፍ የኦነሠ በኦሮሚያ ውስጥ የሚፈጸሙ የንፁሀን ጭፍጨፋዎች በብልፅግና መንግስት በቀጥታና በተዘዋዋሪ የሚፈፀሙ መሆናቸውን ለማጋለጥ የተጠናቀረ የቪዲዮ፣ የድምጽ እና ሌሎች መረጃዎችን መልቀቅ የሚጀምር መሆኑን ከወዲሁ መግለፅ ይፈልጋል።
ፍትህ ሁሌም የበላይ ይሁን! ድል ለኦሮሞ እና ለተጨቆኑ ህዝቦች በሙሉ! የኦነግ-ኦነሠ ከፍተኛው ዕዝ ማርች 5፣ 2022
コメント